የሀገር ውስጥ ዜና

የአረንጓዴ አሻራ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው

By Hailemaryam Tegegn

July 04, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል አለ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) እንዳሉት÷ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በመትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት ይገባል፡፡

መርሐ ግብሩ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው÷ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም አንስተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ማስጀመሩን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ÷በሀገሪቱ ባሉት 23ቱም ማዕከላት መርሐ ግብሩ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የደን ሽፋን ለመጨመር የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ወሳኝ እንደሆነ መጠቀሱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) ሁሉም ሕብረተሰብ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በመሳተፍ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡