የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ከ25 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መንስኤዎች ተለይተዋል

By Abiy Getahun

July 04, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ከ25 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መንስኤዎች ለይቻለሁ አለ።

በሀገሪቱ ከሚከሰተው የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ 47 በመቶ የሚከሰተው በዛፎች ንክኪ በመሆኑ ዛፎች ከመሰረተ ልማቱ የሶስት ሜትር ርቀት ሊኖራቸው እንደሚገባም አመልክቷል።

በክረምት ወራት ሊከሰት የሚችለውን የሀይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ የተሰሩ ሥራዎችን አስመልክቶ አገልግሎቱ በሰጠው መግለጫ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በ152 የመካከለኛ መስመሮች እና እነዚህን መስመሮች የሚሸከሙ 59 ሺህ 48 ምሰሶዎች ላይ ጥልቅ ፍተሻ ተደርጓል ብሏል።

በዚህም ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከባድና ቀላል የሀይል መቆራረጥ መንስኤ የሆኑ የግኝት ነጥቦች ተለይተዋል፡፡

ከግኝቶቹ መካከል 7 ሺህ 277 ቦታዎች ከዛፎች ጋር ንክኪ ያለባቸው፣ 6 ሺህ 367 መቀየር የሚያስፈልጋቸው ምሰሶዎች፣ 2 ሺህ 425 ከግንባታዎችና እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ መስመሮች፣ 6 ሺህ 298 የረገቡ እና የተለያዩ ችግር አለባቸው።

የግኝቶቹን 56 በመቶ ማስተካከል መቻሉን የገለጸው አገልግሎቱ፤ ወደ መሰረተ ልማቱ ተጠግተው ከተገኙ ዛፎች ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ማጽዳት መቻሉን አስታውቋል።

በክረምት ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የሚያጋጥሙ የሀይል መቆራረጥ ችግሮችን የቆይታ ጊዜ ለማሳጠር በቂ ዝግጅት ማድረጉንም አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ 4ኛው ምዕራፍ የኤሌክትሪክ ዲስትሪቢዩሽን መስመሮች መልሶ ግንባታ ስራ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከ625 ኪሎ ሜትር በላይ የእንጨት ምሰሶዎችን ወደ ኮንክሪት ምሰሶ እንዲሁም ሽቦዎችን ወደ ኬብል የመቀየር ስራ ይከናወናል ብሏል፡፡

በተጨማሪም 50 ኪሎ ሜትር መስመሮችን ከመሬት በታች የመቀየር እና የ4 ሺህ ትራንስፎርመሮችን አቅም የማሳደግ ስራ እንደሚከናወን ጠቁሟል።

ከነገ ጀምሮም በሀገር አቀፍ ደረጃ 100 ሺህ ችግኞችን እንደሚተክል የገለጸው አገልግሎቱ፤ ዛፎች ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው ተደርጎ መተከል እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

በመሳፍንት እያዩ

 

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!