አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና የበለጠ ለማጉላት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፡፡
ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት የተቋማዊ ሪፎርም ሥራዎች አፈጻጸም የጋራ መድረክ እየተካሄደ ነው።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የዴሞክራሲ ተቋማት ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
ተቋማቱ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡም በህግና አደረጃጀት ላይ ያሉ ተግዳሮቶች እንዲስተካከሉ የሪፎርም ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማት ለጠንካራ ሀገረመንግስት ግንባታ ያላቸውን ቁልፍ ሚና የበለጠ ለማሳደግ ምክር ቤቱ በአፈጻጸም ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡