የሀገር ውስጥ ዜና

የአረንጓዴ አሻራ የሕዳሴ ግድብን ከደለል ለመከላከል ከፍተኛ ሚና አለው – አቶ አሻድሊ ሃሰን

By Melaku Gedif

July 05, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን የ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በክልሉ ኡራ ወረዳ አስጀምረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሚዛንን ለማስጠበቅና የአፈር ለምነትን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

በክልሉ መርሐ ግብሩ ከተተገበረ ጊዜ ጀምሮ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን ነው አቶ አሻድሊ የተናገሩት፡፡

የሚተከሉ ችግኞች የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ከደለል ለመከላከል የሚከናወኑ ሥራዎችን ግምት ውስጥ ያስገቡ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ባበክር ሃሊፋ በበኩላቸው÷ ለአረንጓዴ አሻራ በክልሉ በሚገኙ 84 የችግኝ ጣቢያዎች 75 ሚሊየን ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይም 60 ሚሊየን የሚጠጉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ተደርገው ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል፡፡

የተዘጋጁት ችግኞች የቡና፣ ደንና ጥምር ደን፣ የእንስሳት መኖ፣ ፍራፍሬ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው እጽዋት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ለችግኝ ተከላ የሚሆኑ 276 ቦታዎች መለየታቸውን ጠቁመው÷ በአጠቃይ 1 ሺህ 354 ሄክታር መሬት ላይ ችግኝ እንደሚተከል ጠቅሰዋል፡፡

መርሐ ግብሩን በስኬት ለማጠናቀቅ የክልሉ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ማቅረባቸውንም የክልሉ ግብርና ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ፈቃዱ ወዬሳ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!