አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቅመማ ቅመም ሰብል ሽፋን ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ ደርሷል ተባለ።
በክልሉ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በኩታ ገጠም እየለማ የሚገኘውን የቅመማ ቅመም ሰብል ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሀላፊ ወ/ሮ በረከት እዮብ÷ በክልሉ ለቅመማ ቅመም በተሰጠው ትኩረት የአርሶ አደሩ የማሳ ሽፋን እያደገ መጥቷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ቋሚና አመታዊ የቅመማ ቅመም ማሣ ሽፋን ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መድረሱንም አስረድተዋል።
በቅመማ ቅመም ከተሸፈነው መሬት በየዓመቱ እስከ 398 ሺህ ቶን ምርት ይገኝ እንደነበር አስታውሰው÷ በ2017 ዓ.ም ከ56 ሺህ ቶን በላይ የቅመማ ቅመም ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል ነው ያሉት።
በቴፒ ከተማ ህብረት ፍሬ ቀበሌ በክላስተር እርድ እያመረቱ የሚገኙ አርሶ አደሮች የቅመማ ቅመም ዋጋ አሁን ላይ ከፍተኛ በመሆኑ የበለጠ ለማምረት መነሳሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸው እንዲሁም የግብርና ግብዓቶች እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡
በተስፋየ ምሬሳ