ቢዝነስ

ከቡና ወጪ ንግድ ከ2 ነጥብ 24 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

By Yonas Getnet

July 07, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ባለፉት 11 ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ከ2 ነጥብ 24 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል አለ።

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ሳህለማርያም ገ/መድህን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ከ280 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ ለመላክ ዕቅድ ተይዞ ነበር።

በዚህም 409 ሺህ 605 ቶን ቡና በመላክ ከዕቅድ በላይ 146 በመቶ በማሳካት ከ2 ነጥብ 24 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት ካለፈው ዓመት አንጻር የ1 ቢሊየን ዶላር ብልጫ መመዝገቡን ተናግረዋል።

ዘንድሮ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና አሜሪካ ቀዳሚ የኢትዮጵያ ቡና ምርት መዳረሻ ሀገራት እንደሆኑ አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ጣልያን እና ዮርዳኖስ የኢትዮጵያን ቡና በብዛት የሚገዙ ሀገራት መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

አክለውም በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር ምርታማነትን ማሳደግ፣ ጥራትን ማስጠበቅ፣ ግብይትን ማዘመን፣ ህገ-ወጥ ንግድን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሳፍንት እያዩ