አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብር አከፋፈል ሥርዓቱ ለግብር ከፋዮች ምቹ እንዲሆን በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል አለ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ዓለምነሽ ደመቀ እንዳሉት÷ የ2018 ግብር ዘመን ዓመታዊ የግብር መክፈያ ቀን ከነገ ጀምሮ በመሆኑ አገልግሎቱን ለመስጠት መደበኛ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግጁ ሆነዋል።
ከዚህ በተጨማሪ 230 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት መደራጀታቸውን ገልጸው፤ ግብር ከፋዮች ግብር ለመክፈል እና የንግድ ሥራ ፍቃድ ለማደስ በአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።
የግብር አሰባሰቡን ሥራ በ10 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡
ወደ ብልፅግና ለሚደረገው ጉዞ ዋነኛ የፋይናንስ መሰረት ለሆነው የግብር አሰባሰብ ውጤታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከግብር የሚሰበሰበው ሀብት ተመልሶ ለህዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እና መንግስታዊ አገልግሎቶችን ወደ ህዝብ ለማድረስ የሚውል በመሆኑ ለግብር መሰብሰብ ሂደት የሁሉም ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደረጃ ”ሀ” ”ለ” እና ”ሐ” 125 ሺህ ግብር ከፋዮች የተመዘገቡ ሲሆን በ2017 ግብር ዘመን በአጠቃላይ 21 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በ11 ወራት ውስጥ ከ18 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ከዚህ መነሻ ዘንድሮም ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ ከደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ብቻ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ባሉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ዓመታዊ ግብር የመክፈል ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመለሰ ታደለ