ፋና ስብስብ

በመጀመሪያ ተልዕኮው የ165 ሰዎችን ህይወት የታደገው ወጣት…

By Hailemaryam Tegegn

July 07, 2025

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ባሳለፍነው ሳምንት በደረሰ የጎርፍ አደጋ 28 ህጻናትን ጨምሮ እስካሁን የ82 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፥ በርካቶች አደጋውን ተከትሎ የገቡበት አልታወቀም፡፡

የነፍስ አድን ሰራተኞች በአደጋው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለግ ስራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ጥረት የ165 ሰዎችን ህይወት የታደገው የነፍስ አድን ባለሙያ እየተሞገሰ ይገኛል፡፡

የአሜሪካ የባህር ሀይል የነፍስ አድን ቡድን አባል የሆነው ስኮት ሩስካን የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ እየተደረገ ባለው ርብርብ 165 ሰዎችን ህይወት መታደጉ ተነግሯል፡፡

ይህን ተከትሎም የሀገር ውስጥ የህዝብ ደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት ክሪስቲ ኖይም ፔቲ ኦፊሰር ስኮት ሩስካንን የአሜሪካ ጀግና ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡

የ26 ዓመቱ ጠላቂ ዋናተኛ የነፍስ አድን ስራውን የተቀላቀለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው ዕለት የአደጋ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የነፍስ አድን ስራ ስልጠናን ተከታትሎ ያጠናቀቀው በቅርቡ መሆኑንና ይህ የነፍስ አድን ተልዕኮ የመጀመሪያው መሆኑን የሚናገረው ስኮት ሩስካን፥ ጀግና የሚል ሙገሳ ከቀረበለት በኋላ በሰጠው አስተያየት፥ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ስራዬ ይኸው ነው፥ ማንም በእዚህ ቦታ ላይ ቢኖር የሚችለውን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፥ እኔም ያደረግኩት የተሰጠኝን ኃላፊነት መወጣት ነው ሲል ለኤቢሲ ኒውስ ተናግሯል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ