አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል እየተካሄደ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረት የመስራት እሴትን አጠናክሯ አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የዘንድሮውን ክልላዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሠመራ ከተማ የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ አስጀምረዋል።
በዚህ ዓመት የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር 170 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ወገኖች ቤት የማደስ ስራ እንደሚከናወን ገልጸው፥ የህዝቡን የመተጋገዝና የመደጋገፍ ነባር እሴት በመጠቀም በክልሉ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐሚድ ዱላ በበኩላቸው፥ በክረምት ወራት በ14 የተለያዩ የበጎ አድራጎት ዘርፎች ከ300 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉባቸው ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
ወጣቶችን በንቃት በማሳተፍ ለሀገራቸው የበኩላቸውን ሚና የሚወጡበትን ተግባር ለማቀላጠፍ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡