የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ 10 ሺህ የቅድመ ክፍያ ስማርት ቆጣሪዎች ገጠማ ተከናወነ

By Melaku Gedif

July 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ 10 ሺህ የቅድመ ክፍያ ስማርት ቆጣሪዎች ገጠማ ሥራ ተከናውኗል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ለቅድመ ክፍያ ካርድ ቆጣሪ ደንበኞች የክፍያና የኢነርጂ ሽያጭ ሥርዓቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍ ፕሮጀክት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

እስካሁንም በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ 10 ሺህ የነጠላ ፌዝና 120 ባለ ሶስት ፌዝ ስማርት ቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች ገጠማ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ መተግበር በዋናነት ከቅድመ ክፍያ የአከፋፈል ሥርዓት እና ከድህረ ክፍያ ንባብ ጋር ያለውን ችግር በመፍታት የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል፡

በተጨማሪም ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው በስልካቸው ኢነርጂ መግዛት እንዲችሉና በተለያየ ምክንያት የማይሰበሰብ ገንዘብን ለማስቀረት እንዲሁም አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡

በፕሮጀክቱ 500 ሺህ ስማርት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን ለመግጠም የታቀደ መሆኑን ጠቁመው ÷ ከዚህ ውስጥ 150 ሺህ የሚሆኑት ስማርት ነጠላ ፌዝ ቆጣሪዎች ናቸው፡፡

350 ሺህዎቹ ደግሞ ነጠላ ፌዝ የኦፍላይን ቆጣሪዎች ናቸው ያሉት አቶ አንዋር÷ በቀጣይ 15 ሺህ ስማርት ነጠላ ፌዝ ተጨማሪ ቆጣሪዎች ገጠማ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደሚተገበር አመልክተዋል፡፡

125 ሺህ የሶስት ፌዝ ስማርት ቆጣሪዎች እና 350 ሺህ የነጠላ ፌዝ ኦፍላይን ቆጣሪዎች ገጠማ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ የመተግበር ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት፡፡

በመላኩ ገድፍ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.) Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook WMCC TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!