አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም የአህጉሪቱ ወጣቶችና ሥራ ፈጣሪዎች ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል አሉ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም የማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕዚዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
በዚህም አማራጭ የሥራ ዕድሎችን የማስፋት፣ በየዘርፉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የማስረጽና ወጣቱ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሥራ ፈጠራ ፎረም የአህጉሪቱ ወጣቶችና ሥራ ፈጣሪዎች ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
ፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት በቀጣይ በዘርፉ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ከማድረግ ባለፈ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀመጡበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ቀጣይነት ያለው ልማትን እንድታረጋግጥ በኢኮኖሚ፣ በልማትና በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር የጋራ ርብርብና ጥረትን የሚጠይቅ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በሥራ እድልና በተለያዩ ዘርፎች ከአህጉሪቱ ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።