የሀገር ውስጥ ዜና

በጎንደር የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው – አቶ ፍቃዱ ተሰማ

By Melaku Gedif

July 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎንደር ከተማ በፌዴራልና በክልሉ መንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው አሉ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ።

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የከተማውን የልማት ሥራዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

አቶ ፍቃዱ ተሰማ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ ለመምጣቱ ማሳያ ናቸው።

የክልሉ ሕዝብ ሠላም ወዳድና ልማት ፈላጊ መሆኑን በቅርቡ ባካሄዳቸው ሰልፎች መልዕክት ማስተላለፉን አመልክተዋል።

የታጠቁ ሃይሎች የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብለው የሠላምን መንገድ አማራጭ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማውን ታሪካዊነት የሚያጎሉና የቱሪዝም ማዕከልነቱን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።

የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት እድሳትና ጥገና ሥራ ታሪክን በመጠበቅ የከተማውን የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

የከተማውን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዳግም ግንባታው የተጀመረው የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ሥራ በጥራትና በፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማት ሥራዎችና የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም የተሻለ የመልማት እድልና ለኑሮ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ እንደሆኑ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡