የሀገር ውስጥ ዜና

ምርጫ ቦርድ ከተካሄዱ ምርጫዎች ተሞክሮ በመውሰድ ማሻሻያዎችን ማቅረቡ ተገቢ ነው – ቋሚ ኮሚቴው

By Melaku Gedif

July 09, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ጊዜያት ከተካሄዱ ምርጫዎች ተሞክሮ በመውሰድ ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማቅረቡ ተገቢ ነው አለ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ቦርዱ በተለያዩ ወቅቶች ከተካሄዱ ምርጫዎች በመነሳትና የውጪ ተሞክሮን በመቀመር የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው።

ቦርዱ ረቂቅ አዋጁን ሲያዘጋጅ በኢትዮጵያ አካታች የፖለቲካ አካሄድ እንዲኖር ለማድረግ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው ÷ በዋናነትም ለወጣቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ሴቶች አካታች እንዲሆን የሰጠውን ትኩረት አድንቀዋል።

በኢትዮጵያ ያለው አዳጊ ዴሞክራሲ በመሆኑ ፓርቲዎች ስህተት በሚፈጥሩበት ጊዜ ማረም ተገቢ መሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢው ÷ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበርም በረቂቅ አዋጁ የተካተቱት ጉዳዮች ተገቢ መሆናቸውን አንስተዋል።

ምርጫን በቴክኖሎጂ ለማከናወን በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ተገቢና አስፈላጊ ከመሆኑ ባለፈ ጊዜውን የዋጀ ነው ብለዋል።

ከቅሬታ ሰሚ አኳያም በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግ ነው ሰብሳቢው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ሃይሉ በበኩላቸው÷ በረቂቅ አዋጁ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት በአፈጻጸም ላይ የታዩ ክፍተቶችን መፍታት የሚያስችል ማሻሻያ መደረጉን አስገንዝበዋል፡፡

የመራጭነትና የዕጩነት ምዝገባና የእድሜ ሁኔታን ያካተቱ አንቀጾች እንደተካተቱበት መናገራቸውንም ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡