የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ102 ሺህ በላይ የክስ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጠ

By Abiy Getahun

July 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ከ102 ሺህ በላይ በሚሆኑ የክስ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ በፍትሐብሔር እና በወንጀል 113 ሺህ 96 መዛግብት ቀርበዋል።

ከእነዚህ ከቀረቡ መዛግብት መካከል 102 ሺህ 713 መዛግብቶች ላይ ውሳኔ በመስጠት የዕቅዱን 91 በመቶ መፈፀም ተችሏል ብለዋል።

10 ሺህ 383 መዝግቦች ደግሞ ወደ ቀጣይ ዓመት መዛወራቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ያለ እድሜ ጋብቻ፣ አስገድዶ መድፈር፣ በሴቶች ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረስ እና ጠለፋ የመሳሰሉ የክስ መዝገቦች በበጀት ዓመቱ በተለየ ሁኔታ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም ህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር፣ የሙስና ጉዳዮች፣ ግብር እና ታክስ ማጭበርበር፣ ኮንትሮባንድ፣ የማዳበሪያ ዕዳ እና የማይክሮ ፋይናንስ ብድር አመላለስ በበጀት ዓመቱ ውሳኔ የተሰጠባቸው መዝገቦች ውስጥ እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።

የዳኞች ዲሲፕሊን፣ የአደረጃጀትና የአሰራር፣ ፍርድ ቤቶች ዝግ በሚሆኑበት ጊዜ ተረኛ ችሎት አመዳደብ እና የፈቃድ አሰጣጥ ደንብ እና መመሪያዎችን የማውጣት ሥራ በበጀት ዓመቱ ተከናውኗል ብለዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመት ፍርድ ቤቱ የውሳኔ አቅሙን በማሳደግ እና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በሚኪያስ አየለ