የሀገር ውስጥ ዜና

ለቅመማ ቅመም ምርት እምቅ አቅም ያለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል…

By Melaku Gedif

July 11, 2025

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለቅመማ ቅመም ምርት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡

በቢሮው የቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቶፊቅ ጁሃር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለቡናና ቅመማ ቅመም ምርት እምቅ አቅምና ምቹ ሁኔታ አለ፡፡

በዚህም መሰረት ክልሉ ለቅመማ ቅመም ምርት ያለውን ጸጋ በጥናት በመለየት በትኩረት መሰራቱን ጠቁመው÷ በ2017 በጀት ዓመት 67 ሺህ ሄክታር መሬት መልማቱን አንስተዋል፡፡

በክልሉ በብዛት ከሚመረቱ ቅመማ ቅመሞች ውስጥ ዝንጅብል፣ ሮዝመሪ፣ በርበሬ፣ ሚጥሚጣ፣ ኮሰረት እና እርድ እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

የዘርፉን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ነው ያብራሩት፡፡

አርሶ አደሮች በቅመማ ቅመም ምርት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ በማበረታታት በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 290 ሺህ ቶን ቅመማ ቅመም ለማምረት ታቅዶ ከዕቅድ በላይ 330 ሺህ ቶን ምርት ለገበያ መቅረቡን አብራርተዋል፡፡

ለውጪ ገበያ ከቀረበ 5 ሺህ 700 ቶን ቅመማ ቅመም ምርትም 12 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

በተለይም የሮዝመሪ ቅመምን ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ በቀጣይ በዘርፉ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለማቅረብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አምራቾች የቅመማ ቅመም ምርት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥና የተሳለጠ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ