የሀገር ውስጥ ዜና

በልማትና መልካም አስተዳደር ላይ የተመዘገበውን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይሰራል – አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ

By Mikias Ayele

July 11, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል በልማትና መልካም አስተዳደር ላይ የተመዘገቡ ውጤታማ ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ።

በጅግጅጋ ከተማ ለአራት ቀናት ሲካሂድ የቆየው የክልሉ ሴክተር ቢሮዎችና የዞን አስተዳደሮች የ2017 እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውጤታማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተከናውነዋል።

በግምገማው የተለዩ ጠንካራ አፈጻጸሞች ላይ በመመርኮዝና ደካማ ጎኖችን በማረም ውጤታማ ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሰረት አመራሩ እንደሚሰራ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መድረኩ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን ለመለየትና የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እቅድ አፈፃፀም ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የተቋማት ተጠያቂነትና ግልፅነትን ማጠናከር እንዲሁም አዲሱን በጀት ዓመት የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ለማጎልበት መድረኩ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም አስተዳደራዊ ቅልጥፍናን ለማሻሻልና በመንግስት ተቋማት ላይ የህዝብን አመኔታ ለማጠናከር መድረኩ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።