የሀገር ውስጥ ዜና

አረንጓዴ አሻራ የአተያይና የአኗኗር ለውጥ ያመጣ ባህል እየሆነ  መጥቷል – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

By Mikias Ayele

July 11, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአተያይና የአኗኗር ለውጥ ያመጣ ባህል እየሆነ መጥቷል አሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፡፡

የአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች ለሰባተኛ ጊዜ ‹‹በመትከል ማንሰራራት›› በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ የሚገኘውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር  ችግኝ በመትከል አከናውነዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ተቋሙ በተከታታይ በተደረጉት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል።

ለዘንድሮወ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ የተመጣጠነ ዝናብ እንድናገኝ፣ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ለመኖር እና በምግብ እራስን ለመቻል የሚረዳ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተር ጀነራሉ÷ ዜጎች በሂደት የራሳቸው ባህል ያደረጉት የአተያይና የአኗኗር ለውጥ ያመጣ ተግባር እየሆነ ይገኛል ብለዋል።

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር በሚገኘው የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የችግኝ ተከላ የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሎች፣ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች መሳተፋቸውን  ተቋሙ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የላከው መረጃ ጠቁሟል፡፡