ዓለምአቀፋዊ ዜና

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠሩ ከ150 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

By Mikias Ayele

July 11, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጀመረ ዘመቻ በስድስት ቀናት ውስጥ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ከ150 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ 43 ሀገሮች የተውጣጡ 15 ሺህ ያህል መኮንኖች በተሳተፉበት በዚህ ዘመቻ፤ ከ1 ሺህ በላይ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ተለይተዋል።

ዘመቻው በዋነኛነት ተደራጅተው የሰዎችን ዝውውር ጨምሮ በወንጀል ድርጊት የሚሳተፉ ቡድኖችን ዒላማ ማድረጉን ቢቢሲ በዘገባው ጠቁሟል።

ቡድኖቹ አዳጊዎችን ለወሲባዊ ብዝበዛ፣ ለወንጀል ድርጊት እና ለልመና ለማሰማራት ይጠቀሙባቸው እንደነበር ተነግሯል።

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሰዎችን ክብር እና ነጻነት የሚያሳጣ ከሰብዓዊነት የወጣ ድርጊት መሆኑን የገለጸው ኢንተርፖል፤ ህጻናት ጭምር በከፍተኛ ደረጃ ሰለባ እየሆኑ መምጣታቸውን አስታውቋል።

ችግሩን ለመከላከል በተጀመረው ዓለም አቀፍ ዘመቻ እስካሁን 158 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ 205 ተጠርጣሪ ግለሰቦች ተለይተው ታውቀዋል።

የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ 1 ሺህ 194 ሰዎችም ተገኝተዋል።