ስፓርት

የክለቦች ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በተገኙበት ዛሬ ይካሄዳል

By abel neway

July 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፈረንሳዩ ፒኤስጂ እና የእንግሊዙ ቼልሲ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት የክለቦች ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፍጻሜ ጨዋታውን ለመመልከት በሜት ላይፍ ስታዲየም እንደሚታደሙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በአዲስ አቀራረብ 32 ቡድኖችን አሳትፎ ውድድሩን የጀመረው የ2025 የክለቦች ዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የእንግሊዝና ፈረንሳይ ክለቦችን ያገናኘው፡፡

በፍጻሜ ጨዋታው በውድድር ዓመቱ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያሳካው ፒኤስጂ እና የኮንፍረንስ ሊግ ዋንጫን ያነሳው ቼልሲ ተጨማሪ ድሎችን ለማግኘት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ፡፡

በፒኤስጂ በኩል የባሎንዶር እጩው ኦስማን ዴምቤሌን ጨምሮ ቪቲኒሃ፣ ዴዚሬ ዱዌ እና ኪቪቻ ካቫርስኬሊያን የመሳሳሉ ክዋክብቶች የሚያደርጉት ፍልሚያ በስፖርት ማሕበረሰቡ ዘንድ ትኩረት ስቧል፡፡

በተመሳሳይ የቼልሲ አዲሱ ፈራሚ ጆዓኦ ፔድሮ፣ ኤንዞ ፈርናንዴዝ እና ፖል ፓልመር ለክለባቸው ተጨማሪ ዋንጫ ለማስገኘት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይጠበቃል፡፡