አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባሕር ዳር ከተማ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
መርሐ ግብሩን የአማራ ልማት ማሕበር (አልማ)፣ የባሕር ዳር ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡
“ለአልማ እሮጣለሁ ማኅበራዊ ሃላፊነቴን እወጣለሁ”በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ አትሌቶች፣ ወጣቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ም/ከንቲባ አስሜ ብርሌ በዚህ ወቅት÷ የከተማዋ የኮሪደር ልማት ማኅበረሰቡ በእረፍት ጊዜው የጎዳና ላይ ሩጫና ሌሎች ስፖርቶችን በማከናወን ጤናውን እንዲጠብቅ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
አልማ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለማሳደግ ያስጀመረው ስፖርታዊ ንቅናቄ በሌሎች ተቋማትና ማኅበራት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የአልማ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበረ መኩሪያ በበኩላቸው÷ ማህበሩ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን አባላትን እና ከ97 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን ይዞ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ሃብት ከማኅበረሰቡና ከተቋማት በማሰባሰብ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫው የማኅበረሰቡን፣ የአባላቱንና በጎ ፈቃደኞችን ተሳትፎ በማሳደግ ሕብረቱን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በውድድሩ በወንዶች ምድብ አትሌት ሃብታሙ ፈንታሁን እንዲሁም በሴቶች አትሌት ሰላም ካሴ አሸንፈዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ