አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን በ2018 በጀት ዓመት ለማስቀጠል በሃሳብ አንድነትና ትብብር መስራት ይገባል አሉ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት የተሟላ የሁሉም ዘርፎች እቅድ እና የሀገራዊ የልማት እቅድ ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም በኢትዮጵያ ታሪክ ከተመዘገቡ የኢኮኖሚ ውጤት በእጅጉ የላቅ ነው፡፡
በ2017 የበጀት ዓመት የመጀመሪያው ሳምንት የዓመቱ የሥራ ክንውን እውነተኛ የታሪክ እጥፋት የሚያመጣና ለኢትዮጵያ ማንሰራራት መሰረት የሚጥል እንዲሆን በሚል ካቢኔው የዓመቱን እቅድ ተወያይቶ የሃሳብ ጥራት ይዞ በጋራ ርብርብ መጀመሩን አስታውሰዋል።
በዚህም የወጪ ንግድ ውጤታችን በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ካለፈው ዓመት ከእጥፍ በላይ መሆኑንና ከገቢ አንጻርም ወደ እጥፍ የቀረበ ከፍተኛ እመርታ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
የዋጋ ግሽበት በግማሽ የቀነሰበት እና በአገልግሎት ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የመሶብ ማዕከል በሀገር ውስጥ ልጆች ተሰርቶ ሥራ የጀመረበት ዓመት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በሪፎርሙ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይሲቲ ዘርፎች በጣም ተስፋ ሰጪ ውጤት መጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ በማህበራዊ፣ በትምህርት እና ጤና ዘርፎች አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ጠቅሰዋል፡፡
አጠቃላይ በዚህ ዓመት የመንግስት አፈጻጸም ከዚህ ቀደም ከነበረው ውጤት በእጅጉ የላቀና የሚያበረታታ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ነገር ግን ይሄው ጅማሮ በ2018 ዓ.ም ካልተደገመ የተሟላ እንደማይሆን አንስተው ÷ ውጤቱን መደጋገም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ቀጣዩ ዓመት ጥራት ያለው የጋራ ሃሳብ ፣ ዕቅድ እንዲሁም የተደመረ ክንድ እንደሚፈልግ ነው የተናገሩት፡፡
በእቅዳችን ላይ ከተወያየን በኋላ በየዘርፉ በሚደረገው ርብርብ የዚህ ዓመት ውጤት እንደባለፈው ዓመት የተሳካ ከሆነ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የመውሰድ እድላችን በጣም የሰፋ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በሕዳሴ ግድብ፣ በበርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ፣ በኮሪደር ልማት ፣ በገጠር ኮሪደር ልማት እና ሌሎች ኢንሼቲቮች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ጠንካራና ትጉህ አመራር እንደሚፈልጉ እና ካቢኔው በተሟላ መንገድ ተገንዝቦ አመራር መስጠት ከቻለ የ2017 ዓ.ም ውጤትን በቀጣዩ ዓመትም መድገም እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡
የዛሬው መድረክ የጋራ ሃሳብ ለመያዝ መዘጋጀቱን ጠቁመው ÷ አጀንዳዎቹም የሚቀጥለውን ዓመት እቅድ የማየት እና አጽድቆ ለሥራ መዘጋጀት ናቸው ብለዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት