ስፓርት

ቼልሲ ሮማን አብራሞቪችን ካጣ በኋላ ወደ ስኬት የተመለሰበት ዓመት…

By Abiy Getahun

July 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሩሲያዊው ባለሃብት ሮማን አብራሞቪች ቼልሲን ለአሜሪካዊው ባለሃብት ከሸጡ በኋላ ይህ ቡድን በርካታ ተጫዋቾችን በውድ ገንዘብ ወደ ስብስቡ ቢቀላቅልም ስኬታማ ሳይሆን ቆይቷል፡፡

ቼልሲ በአሜሪካዊው ባለሃብት ቶድ ቦህሊ ከተያዘ በኋላ በሊጉም ሆነ በሌሎች ውድድሮች ላይ ስኬታማ ጊዜን ለማሳለፍ ሲቸገር ቆይቷል፡፡ በዚህ የውድድር ዓመት ግን የኮንፍረንስ ሊግ ዋንጫን እና የክለቦች ዓለም ዋንጫን በማሳካት ከስኬታ ጋር መገናኘት ጀምሯል፡፡

በወጣት ተጫዋቾች እየተገነባ የሚገኘው ቡድኑ በ2025 ሁለት ዋንጫዎች ከማሳካት ባለፈ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆን ችሏል፡፡

በኢንዞ ማሬስካ የሚመራው ቡድኑ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ቡድኖች መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችል በክለቦች ዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ አሳይቷል፡፡

በክለቦች ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የወቅቱ ምርጥ ቡድን እና የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ አሸናፊውን የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂን ከጨዋታ ብልጫ ጋር ያሸነፈበት መንገድ ቡድኑ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን ያሳየ ሆኖ አልፏል፡፡

ጣልያናዊው አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ በስታምፎርድ ብሪጅ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን ቆይታቸው የኮንፍረንስ ሊግ እና የክለቦች ዓለም ዋንጫን ማሳካት ችለዋል፡፡

አሁን በቡድኑ ውስጥ የሚገኙት ተጫዋቾች ወጣት እንደመሆናቸው በሚቀጥሉት ዓመታት በዚህ ቡድን ውስጥ ጥሩ ጊዜን ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኮል ፓልመር፣ ካይሴዶ፣ ኢንዞ ፈርናንዴዝ፣ ፔድሮ እና ሌሎች የቡድኑ ተጫዋቾች በዚህ ቡድን ውስጥ ድንቅ እንቅስቃሴ እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ሩሲያዊው ባለሃብት በፈረንጆቹ 2022 ይህንን ክለብ ከለቀቁ በኋላ ከእሳቸው ክለቡን የገዙት አሜሪካዊው ባለሃብት ቶድ ቦህሊ ለተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ገንዘብ ሲያወጡ ቢቆዩም ከዋንጫ ጋር ለመገናኘት እና ቡድኑን ወደቀድሞ ስሙ ለመመለስ ብዙ መስራት ግድ ብሏቸው ነበር፡፡

አሜሪካዊው ባለሃብት ቶድ ቦህሊ ለተጫዋቾች ዝውውር ብዙ ገንዘብ ቢያወጡም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተጫዋቾ ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ ካገኙ ቡድኖች መካከል ቼልሲ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ነው፡፡

በአብራሞቪች ዘመን ይህ ቡድን የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ክብሮችን ማሳካት መቻሉ አይዘነጋም፡፡ አሁን በቶድ ቦህሊ ስር ዋንጫዎችን ማሳካት የጀመረው ቡድኑ በቀጣይም በሌሎች ውድድሮች ይጠበቃል፡፡

ቼልሲ ትልልቅ የሚባሉትን ሁሉንም ዋንጫዎች በማሳካት የመጀመሪያው ክለብ ሲሆን÷ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የክለቦች ዓለም ዋንጫ፣ ዩሮፓ ሊግ፣ ካራቦ ካፕ፣ ኤፍ ኤ ካፕ እና የኮንፍረንስ ሊግ ዋንጫዎችን ከፍ አድርጎ ማንሳት ችሏል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!