የሀገር ውስጥ ዜና

ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል የተዘጋጀው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

By Adimasu Aragawu

July 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅቷል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የኮርፖሬሽኑን 7ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ጋር በመሆን በቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዛሬ አስጀምረዋል።

ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት ዓመታት ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ችግኞችን አፍልቶ በመትከል በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተሳትፎ አድርጓል።

እንዲሁም ለተቋማትና ከተማ አስተዳደሮች ጭምር ችግኝ በማቅረብ እንዲተከሉ አድርጓል ነው ያሉት።

ዘንድሮም በአስር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች፣ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ የተዘጋጁ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።

በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ኮርፖሬሽኑ በስሩ በሚያስተዳድራቸው ፓርኮችና ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች 10 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በራስ አቅም አዘጋጅቷል፡፡

በዚህም ችግኞችን በማፍላት ከመትከል በተጨማሪ በየአካባቢያቸው ላሉ ተቋማት ማከፋፈል ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ይህም ኮርፖሬሽኑ ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጠውን ትኩረት የበለጠ እንዲያጠናክር ይረዳዋል ነው ያሉት፡፡

በአድማሱ አራጋው