የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በፖሊሲ የታገዙ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም ተሞክሮዋን የምታጋራበት መድረክ

By abel neway

July 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ በፖሊሲ የታገዙ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም ተሞክሮዋን የምታጋራበት መድረክ ይሆናል አለ።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ታስተናግዳለች።

ጉባኤውን አስመልክቶ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን፣ ለጋሽ ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደች ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን፥ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የታዳሽ ሀይል ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በፖሊሲ የታገዙ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተግባራትን በማከናወን ተጨባጭ ውጤት ማምጣቷን ገልጸው፤ ይህንን ተሞክሮዋን በጉባኤው እንደምታጋራ ተናግረዋል።

ከሌሎችም ልምዶችን የምትቀስምበት ዕድል እንደሚፈጠርም አመላክተዋል።

በመሆኑም ጉባኤው የተሳካና የአፍሪካን መፃኢ ዕድሎችን የሚያመላክት እንዲሆን የዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን፣ ለጋሽ ተቋማትና የሲቪል ማህበሰረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን እንዲያጎሉ ጠይቀዋል።

ጉባኤው ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም “የአረንጓዴ ጉዳይ ውይይቶች አረንጓዴን ማዕከል ያደረጉ እርምጃዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።