የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ተጠያቂነት ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ ደስታ ሌዳሞ

By Hailemaryam Tegegn

July 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የተጠያቂነት ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉን 2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን፥ በበጀት ዓመቱ ከ18 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በተለያዩ አማራጮች ከሚከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ጎን ለጎን የተጠያቂነት ስራውን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የቤተሰብ ብልፅግናን እውን ለማድረግና ህዝባችንን ከተረጂነት ለማላቀቅ ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸው፥ ከ258 ሺህ በላይ የእንሰሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል፣ የንብ ቀፎዎችን ወደ 158 ሺህ ለማሳደግ መታቀዱን አንስተዋል፡፡

የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የግብር ከፋዮችን ቁጥር ከፍ ለማድረግና ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብና ኢንተርፕራይዞችን ለማስፋፋት መታቀዱንም ነው ያነሱት፡፡

በክልሉ ከ29 ሺህ በላይ ወጣቶችን በቴክኒክና ሙያ ለማሰልጠን ታቅዷል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት በክልሉ 70 አዳዲስ የውሀ ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ሌሎች ነባር ፕሮጀክቶችን ለማደስ መታቀዱን የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን በሙሉ ወደ ትምህርት ገበታ ለማስገባትና ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ለማድረስ ታቅዷል፡፡

በ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍል ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ከ50 በመቶ በላይ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራም ነው የተገለጸው፡፡