የሀገር ውስጥ ዜና

በዓለም አቀፍ ገበያ የቡናና የወርቅ ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ዕድሉን መጠቀም ይገባል – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

By abel neway

July 16, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፉ ገበያ የወርቅና ቡና ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ምርቶቹን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ዕድሉን መጠቀም ይገባል አሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፡፡

በ2018 ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ላይ ገለጻ ያደረጉት ሚኒስትሯ፤ በፈረንጆቹ 2025 አንድ ኪሎ የአረቢካ ቡና በዓለም አቀፉ ገበያ 8 ነጥብ 7 የአሜሪካን ዶላር ነው ብለዋል።

በ2026 ወደ 7 ዶላር ቢወርድም የተሻለ ዋጋ ሆኖ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በመሆኑም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር እንዲሁም ከሎጂስቲክስ ጋር የሚገናኙ ችግሮችን በመቅረፍ የቡና ምርትን ለዓለም አቀፍ ገበያ በስፋት ማቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በጥር፣ መጋቢትና ግንቦት 2025 የአንድ ወቄት የወርቅ ዋጋ 3 ሺህ 300 ዶላር ማውጣት ችሏል ነው ያሉት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)።

የዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ከታሪፍ ጭማሪ ጋር በተገናኘ መቀዛቀዝ እያሳየ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ወርቅ ላይ ስለሚያውሉ ኢትዮጵያ ምርቱን በስፋት ለገበያ በማቅረብ ዕድሉን መጠቀም ይገባታል ብለዋል።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ወደ ሀገር ውስጥ የምታስገባቸው የአልሙኒየምና ብረታ ብረት ምርቶች በ2025 የተወሰነ ቅናሽ እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና የሪል ስቴት ዘርፉ መነቃቃት በማሳየቱ የአልሙኒየምና ብረታ ብረት ምርቶች ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ዋጋቸው ሊጨምር ስለሚችል ምርቶቹን በሀገር ውስጥ የመተካት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአቤል ንዋይ