አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከቴሪ ኦንሪ እስከ አለን ሺረር፣ ከማይክል ኦውን እስከ ፊሊፖ ኢንዛጊ በሜዳ ውስጥ እሱን በተቃራኒ መግጠም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በአደባባይ መስክረውለታል።
የማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞ ተጫዋች የነበረው የሀገሩ ልጅ ቫን ኒስትሮይ በልምምድ ሜዳም ቢሆን ያፕ ስታምን መግጠም ፈታኝ መሆኑን መናገሩ አይዘነጋም።
ማንቼስተር ዩናይትድን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ያፕ ስታም ፍርሃትን የማያውቅ ምህረት የለሽ ተከላካይ ስለመሆኑ አብረዉት የተጫወቱ እና በተቃራኒ የገጠማቸው ተጫዋቾች መስክረውለታል።
የማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በወቅቱ እሱ እንዲሄድ በመፍቀዴ ትክክለኛውን ስራ የሰራሁ መስሎኝ ነበር ነገር ግን ተሳስቻለሁ፤ ያፕ ስታም በጣም ጥሩ ተከላካይ ነው እሱን በማጣቴ ተጸጽቻለው በማለት ተናግረዋል።
ፈርጉሰን ያፕ ስታምን ለመሸጥ የወሰኑት ውሳኔ ርህራሄ የለሽ ውሳኔ ነው በማለት ፖል ስኮልስ እና ኒኪ በት ውሳኔያቸውን ተችተው ነበር።
የማንቼስተር ዩናይትድ የቀድሞ ተጫዋች ሮይ ኪን፤ እንደ ሚሰማር ከባድ የሆነው ስታም የተከላካይ ክፍላችንን ብረት አድርጎት ነበር በማለት አድናቆቱን ገልጾ እሱን በማጣታቸው ብዙ መጎዳታቸውን ይናገራል።
ሪያን ጊግስ በበከሉ ያፕ ስታም በጣም አስፈሪ እና ከባድ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ነው ሲል አድናቆቱን ገልጾለታል።
በብዙዎች በአደባባይ ስለችሎታው የተመሰከረለት ያፕ ስታም በማንቼስተር ዩናይትድ ቤት አሻራቸውን አሳርፈው ካለፉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡
ኔዘርላንዳዊው የቀድሞ ኮከብ በተጫዋችነት ዘመኑ ከፒኤስቪ አይንዶቨን የእንግሊዙን ክለብ ማንቼስተር ዩናይትድን በመቀላቀል ስኬታማ የውድድር ዓመታትን አሳልፏል፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድ በአሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን እየተመራ በፈረንጆቹ 1999 የውድድር ዓመት የሶስትዮሽ ክብርን ሲጎናፀፍ ያፕ ስታም የስብስቡ አካል ነበር፡፡
ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር 3 ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት የቻለው ተከላከዩ የኤር ዲቪዜ እና የኮፓ ኢታሊያ ዋንጫዎችንም አሳክቷል፡፡
ከምንግዜም ምርጥ የመሀል ተከላካዮች መካከል አንዱ የሆነው ኔዘርላንዳዊው ያፕ ስታም በፈረንጆቹ 1997 የኔዘርላንድስ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመባል የተመረጠ ሲሆን በ1998/99 እና በ1999/2000 የውድድር ዓመታት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋቾች ስብስብ ውስጥ ተካትቷል፡፡
ለሀገሩ ኔዘርላንድስ 67 ጨዋታዎችን አድርጎ 3 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን በክለብ ደረጃ 415 ጨዋታዎችን አድርጎ 23 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ከፒኤስቪ አይንዶቨን ማንቼስተር ዩናይትድን ከተቀላቀለ በኋላ በቀያይ ሴጣኖቹ ቤት ጥሩ ጊዜን አሳልፎ ቀጣይ መዳረሻውን ጣሊያን በማድረግ ለላዚዮ እና ኤሲሚላን ተጫውቷል፡፡
ከዚያም ወደ ኤርዲቪዜ በመመለስ በአያክስ አምስተርዳም ቤት በፈረንጆቹ 2007 የውድድር ዓመት የተጫዋችነት ዘመኑን ቋጭቷል፡፡
በፈረንጆቹ 2007 ራሱን ከእግር ኳሱ ዓለም ያገለለው ያፕ ስታም ብዙም ሳይቆይ በ2009 ጊዜያዊ አሰልጣኝ በመሆን የአሰልጣኝነት ስራውን ጀምሯል፡፡
ከዚያ በኋላ በአሰልጣኝት ህይወቱ ፌይኖርድን ጨምሮ የተለያዩ ክለቦችን ማሰልጠን የቻለው ያፕ ስታም አሁን በተወለደባት ኔዘርላንድስ ፕሮፌሽናል ሊግ ላይ የማይገኘውን ዶስ ካምፔን እግር ኳስ ቡድንን እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
ዛሬ 53ኛ ዓመት የልደት በዓሉን እያከበረ የሚገኘው የቀድሞ ኮከብ ሁለት ሴት ልጆች እና መንታ ወንድ ልጆች አሉት፡፡
ማንቼስተር ዩናይትድን ጨምሮ በተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ያፕ ስታም ልክ በዛሬዋ ዕለት በፈረንጆቹ ጁላይ 17/1972 ነበር ወደዚች ምድር የመጣው፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ