አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ በአግባቡ እንዲከፈል አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነው አለ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር፡፡
የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አባተ ምትኩ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የግል ሠራተኞችን የጡረታ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም ሠራተኞች የሥራ አገልግሎት መረጃቸውን በወቅቱ እና በጊዜ እንዲያቀርቡ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት 24 ሺህ 371 ድርጅቶች እና 216 ሺህ 234 ሠራተኞችን ለመመዝገብ ታቅዶ 25 ሺህ 860 ድርጅቶችና 208 ሺህ 147 ሠራተኞችን መመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በድርጅት 38 በመቶ እና በሠራተኛ 25 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
አንዳንድ ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን የጡረታ መዋጮ በአግባቡ ስለማይከፍሉ ተገቢውን ክትትል በማድረግ አስፈላጊው ርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል፡፡
የግል ድርጅቶች የጡረታ መዋጮ ዓላማን ተገንዝበው ለሠራተኞቻቸው በትክክለኛ ሰዓት ተገቢውን የጡረታ መዋጮ ክፍያ እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓመቱ 40 ቢሊየን ብር የጡረታ ፈንድ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ40 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል።
ከዚህ በፊት በ3 እና በ4 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የጡረታ አበል ጭማሪ ይደረግ እንደነበር አንስተው÷ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ግን በኑሮ ውድነትና ሌሎች ምክንያቶች በየዓመቱ እየተጨመረ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ዘንድሮም ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ጀምሮ ለግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ አበል ጭማሪ መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡
ለአብነትም ዝቅተኛው የጡረታ አበል 3 ሺህ113 የነበረው 50 በመቶ የሚሆን ጭማሪ ተደርጎለት 4 ሺህ 669 ብር መድረሱን አስረድተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ