አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በዲጂታል ስርዓቱ ላይ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በኢትዮጵያ መንግስት የሚመራ ኢኒሼቲቭ ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍ እና የልማት ኤጀንሲ ተዋንያንን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ መሰረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነትን በመለየት የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ ያሳልጣል።
የዘርፉ ምሁራን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ተቋማት ከወረቀት አሠራር እንዲወጡ አስችሏል።
በተጨማሪም የመንግሥትን የኤሌክትሮኒክ ግዥ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የዲጂታል ስርዓት ፈጥሯል ነው ያሉት።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥራ አስፈፃሚ ሀብታሙ ፋንታ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ በቴሌ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግና በሌሎች ዲጂታል አማራጮች የሚሰጡ አገልግሎቶች መስፋፋታቸው ለውጤቱ ትልቅ ማሳያ ናቸው።
የፋይናንስ ስርዓቱን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የኢትዮጵያን ዲጂታል ሽግግር ያፋጠኑ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር እና የኮምፒውተር ሳይንስ መምህር ቡልቡላ ኩሜዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዜጎች ኑሮን የሚያቀሉ መረጃዎች በቀላሉ እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከህዝብ ኑሮ ጋር በቀጥታ የተያያዙ የዲጂታል ይዘቶችን እና አገልግሎቶችን ከማልማት አንጻር የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጠቀሱት ምሁራኑ÷ የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ የሚቻለው የአሰራር ስርዓትን በኢኖቬሽን፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መደገፍ ሲቻል መሆኑን ጠቁመዋል።
ተለዋዋጩን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
በአስጨናቂ ጉዱ