አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እውቀትን በማስፋፋት፣ የግለሰቦችንና የተቋማትን የመፈጸም አቅም የማጎልበት ቁልፍ ዓላማ አለው አሉ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ይገኛል።
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 “በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የተገኙ ስኬቶች ላይ ተመስርቶ አዳዲስ የዘርፉ እድገቶች ላይ ያተኮረ ነው።
ስትራቴጂው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ፣ ስማርት ከተሞች፣ ድንበር ተሻጋሪ ኢ-ኮሜርስ፣ ዲጂታል ሉዓላዊነትን የመሳሰሉ ጽንሰ ሃሳቦችን በማካተት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ስለሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች፣ አካታች እና ፍትሃዊ ልማትን እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዓላማ ማድረጉን ማናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዲጂታል እውቀትን በማስፋፋት እና የተቋም አቅምን በመገንባት የግለሰቦችን እንዲሁም የተቋማትን የመፈጸም አቅም ማጎልበት የስትራቴጂው ዋና ዓላማዎች ናቸው ሲሉ ጠቅሰዋል።
አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ማፋጠን፣ ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ተደራሽነትን ማሳደግ እና ኢትዮጵያን ለዲጂታል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን ማድረግም የስትራቴጂው ዓላማ መሆኑን አክለዋል።
ሀገራዊ ዳታዎችንና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አዝማሚያዎችን እና ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን በማሰባሰብና በመተንተን የዲጂታል ልማት ምሰሶዎችንና የትኩረት አቅጣጫዎችን ለይቷል ነው ያሉት።