አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ አሁንም መንግስት የሰላም ጥሪውን ያቀርባል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ።
6ኛው ጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉን የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እያቀረቡ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት ሲያደርግ የነበረው የሰላም ጥሪ አበረታች ውጤት አምጥቷል።
በዚህም የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መንግስት አሁንም የሰላም ጥሪውን ያቀርባል ብለዋል።
በክልሉ ሁሉን አቀፍ እድገት መምጣቱን ገልጸው፤ በግብርና፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና በሌሎች መስኮች በበጀት ዓመቱ ስኬታማ ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።
በክልሉ በዓመቱ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የስራ እድል መፈጠሩን አንስተው፤ የስራ እድል ለተፈጠረላቸው የስራ ማስኬጃ የ14 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብድር መመቻቸቱን ተናግረዋል።
እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት በተከወነ ስራ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን የሚጠጋ ብር በሙስና ተይዞ እገዳ የተጣለበት መሆኑንና 1 ነጥብ 5 ቢሊየን የሚሆነው ተመላሽ መደረጉን አብራርተዋል።
ከገቢ አንጻርም ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ 84 ነጥብ 3 በመቶ ወይም 173 ነጥብ 24 ቢሊየን ብር በዓመቱ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
በቡሳ ጎኖፋ በኩል በተሰራ ስራ አባላትን ወደ 27 ሚሊየን በማሳደግ 14 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል ብለዋል።
በአጠቃላይ በትምህርት፣ በመንገድ ዝርጋታ፣ በውሃ ተደራሽነትና በሌሎችም የልማት አጀንዳዎች አመርቂ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ በ2018 በጀት ዓመትም ስራዎቹን አጠናክሮ በማስቀጠል ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በታምራት ደለሊ