የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ሙያዊ ግዴታቸውን ባልተወጡ 394 ዳኞች ላይ ርምጃ ተወሰደ

By Melaku Gedif

July 20, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዳኝነት ሥርዓት በጎደላቸው 394 ዳኛዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል አለ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፡፡

የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ገዛሊ አባሲመል በ6ኛው ጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ እንዳሉት ÷ በ2017 በጀት ዓመት ፍትሕን ለማስፈንና የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳለጥ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በዚህም የፍርድ ሥራ ሒደቶችን ወደ ዲጂታል አሰራር በመቀየር የተገልጋዩን እንግልት መቀነስ መቻሉን ነው ያብራሩት፡፡

ከወረቀት ነጻ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት 1 ነጥብ 275 ሚሊየን በላይ መዝገቦች ወደ ሶፍት ኮፒ የተቀየሩ ሲሆን÷ከባለፈው ዓመት ጋር 1 ነጥብ 513 ሚሊየን በላይ መዝገቦች ወደ ዳታ ቁጥጥር ሥርዓት ገብተዋል ብለዋል፡፡

በክልሉ የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍ/ቤቶችን ጫና የሚያቀሉ ሥራዎች መከወናቸውን አንስተው÷ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር የሚረዱ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡

በሶስቱም ፍርድ ቤቶች 33 ሺህ 519 ለሚሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ነጻ የጠበቃ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ተዓማኒ መሆኑን ከተገልጋዩ ለማወቅ በተደረገ ጥረት አጥጋቢነቱ 85 ነጥብ 33 በመቶ እንዲሁም ተአማኒነቱ 86 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከፍርድ ሒደቱ ያፈነገጠ ተግባር በሚያከናውኑና ሙያዊ ግዴታቸውን ባልተወጡ 394 ዳኞች ላይ ርምጃ መወሰዱንም አብራርተዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ 29 የሚሆኑ ዳኞች ሙያዊ ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ከሥራ እንዲታገዱ በዳኞች ማህበር አስተዳደር የተወሰነ በመሆኑ የመጨረሻ ውሳኔን እንዲያፀድቅ ለጨፌው አባላት አቅርበዋል።

በታምራት ደለሊ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!