የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን ለማድረግ ከወጣቱ የላቀ አስተዋጽኦ ይጠበቃል

By Hailemaryam Tegegn

July 20, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን አልምቶ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን ለማድረግ በሚሰራው ሥራ ከወጣቱ የላቀ አስተዋጽኦ ይጠበቃል አሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ።

ርዕሰ መስተዳድሯ ከወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ጋር በጋምቤላ ከተማ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።

ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር የብልጽግና ጉዞን ማሳካት የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መኖሩን ተናግረዋል።

መንግስት በየአካባቢው ያሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎች በማልማት የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር እየተከናወኑ ባሉ የልማት፣ የሰላምና የአብሮነት ግንባታ ሥራዎች ወጣቱን በማሳተፍ የታለመውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ለሀገር ልማትና እድገት ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ፥ ወጣቶች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ለሰላም ግንባታ ሥራዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።