የሀገር ውስጥ ዜና

በሚቀጥሉት ቀናት የተለያዩ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ይኖራቸዋል

By sosina alemayehu

July 22, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚቀጥሉት አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ እና በመካከለኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ይኖራቸዋል አለ።

ኢንስቲትዩቱ ለፋና ዲጂታል በላከው የአየር ሁኔታ አዝማሚያ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የሚጠበቀው እርጥበት ለግብርና ሥራ እንቅስቃሴ በአመዛኙ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።

በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ እና በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከመካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚኖራቸው ጠቁሟል።

በአብዛኛው ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖርም አመልክቷል።

ተደጋጋሚ ከባድ ዝናብ ስለሚኖር ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ እንደሚኖር አስጠንቅቋል።

እንዲሁም የወንዞች ከፍታ መጨመር በላይኛው ተፋሰስ በሚነሱ ወንዞች በታችኛው ተፋሰሶች ላይ የወንዞች መጥለቅለቅ ሊያስከትል ይችላል ብሏል።

በመሆኑም በወንዝ ዳርቻ እንዲሁም ረግረጋማ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገንዝቧል።