አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ፅ/ቤት የፕሮቶኮል ኃላፊን ጨምሮ በአስተዳደሩ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች በቀረበባቸው ተደራራቢ ክስ ጥፋተኛ ሆነዉ በመገኘታቸዉ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጡ፡፡
የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የፕሮቶኮል ኃላፊ የነበረችው ኤልቤቴል ሃብቴ፣ የአ/አ አሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ቂርቆስ ክ/ከተማ ጽ/ቤት የተሸከርካሪ መረጃ አጠናቃሪ ባለሙያን ጨምሮ 12 ናቸዉ።
በተከሳሾቹ ላይ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል፣ ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ምንጩን ለመደበቅ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚሉ ተደራራቢ ክሶችን ዐቃቤ ሕግ አቅርቦባቸዋል።
በአንደኛው ክስ ላይ 1ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ በቀረበው ዝርዝር ክስ እንደተመላከተው፤ 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች የአሽከርከሪ ተሸከርካሪ ፍቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን በ2010 ዓ.ም ያወጣውን መመሪያና አሰራር በመተላለፍ በሌላ ሰው ስም የተመዘገበ የተሽከርካሪ የሻንሲ ቁጥር በመቀየር ሊብሬ እና ሰሌዳ ቁጥር በህገ ወጥ መንገድ 1ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች እንዲወስዱ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።
1ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ደግሞ የሻንሲ ቁጥሩን ያስቀየሩትና ሊብሬና ታርጋ በህገ ወጥ መንገድ የወሰዱበትን ተሽከርካሪ ለ3ኛ ወገን በማስያዥያነት በመስጠት የማይገባቸውን 3 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት በማግኘት በግል ተበዳዮች ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ በዋና የሙስና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ወንጀል ተካፋይነት ስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በሁለተኛው ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ 6ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ በቀረበው ክስ ተከሳሾች በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም የግል ተበዳይ ከሆኑት ከ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ጋር በመተዋወቅ 1ኛ ተከሳሽ ከንቲባ ጽ/ቤት የምትሰራ መሆኑን እና ”ቢ.ኢ.ኢ.ኤም ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተባለ ድርጅት በቤተሰብ አቋቁመን ከውጭ ሀገር ዕቃ እናስመጣለን” በማለት የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ስም በመጥቀስ “ጨረታ ከእነሱ ጋር እናመቻቻለን፣ ወንድሜ ዕቃ ከውጭ እያመጣ አትራፊ ነው ከእኛ ጋር ስሩ” በማለት አሳሳች የማግባቢያ ቃላት መጠቀሟ በክሱ ተገልጿል።
በተጨማሪም ተከሳሾቹ አሳሳች ፍሬ ነገር በመግለፅ የግል ተበዳዮች እምነት እንዲጨምር በማድረግ 1ኛ ተከሳሽ ቤታቸው በመሄድ የጎማ ጨረታ ኤልሻዳይ የተባለ ድርጅት ለማቅረብ አሸንፈን ከፍተኛ ገንዘብ አስይዘን 14 ሚሊየን ብር የጎደለን ስለሆነ ያስያዝነዉን ከፍተኛ ገንዘብ ልንበላ ነዉ አብረን ስለምንሰራ ይሄንን የጎደለንን ገንዘብ ስጡን በማለት የጠየቀች መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል።
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የግል ተበዳይ የሆኑትን ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተገለፁትን የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የሆኑትን የግል ተበዳዮችን በማታለል፣ በማስፈራራት ጭምር የሌላ ሰው ንብረት የሆኑትን ተሸከርካሪዎች በማስያዝ በሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም አታለዉ ከግለሰቦቹ በተለያዩ መጠኖች አጠቃላይ 14 ሚሊየን ብር ገንዘብ በመውሰድ በግል ተበዳዮች ላይ ጉዳት ያደረሱ መሆናቸዉ ተጠቅሶ በከባድ የአታላይነት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በ3ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ፣ ከ6ኛ እስከ 12ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሳቸዉ ወይም ለሌላ ሰዉ ለማስገኘት በማሰብ የካቲት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ የግል ተበዳይ የሆኑ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን በተለያየ ቀን እና ቦታ በማግኘት 6ኛ ተከሳሽ የኬ.ኬ አስመጪና ንግድ ሥራ የተባለ ድርጅት ባለቤት ሆኖ ጀነሬተሮች፣ የህትመት ዕቃዎች፣ የኪችን ዕቃ፣ የመኪና ጎማ፣ የመኪና መለዋወጫ፣ ጌጣጌጦች ከውጭ ሀገር በማስመጣት ስራ እንደሚሰራ በሀሰት መናገሩ በክሱ ተጠቅሷል።
1ኛ፣ ከ6ኛ እና እስከ 12ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ጋር በመሆን የግል ተበዳይ የሆኑትን ግለሰቦችን የመኪና ጎማን ጨምሮ የተለያዩ እቃዎችን ከውጭ እናስመጣለን በማለት በማታለል ንግድ ፍቃድ በማሳየት፣ ያሳገዱትን እና ያዘጉትን የተለያዩ ቼኮችን ለመተማመኛ የሚል በመስጠት አታለዉ 30 ሚሊየን ብር በላይ የወሰዱ እና በግል ተበዳዮቹ መታለላቸውን አውቀው ገንዘባችንን ስጡን ብለው ሲጠይቁ ለውይይት በማለት በሆቴሎች በመጥራት ሲያስፈራሯቸው እንደነበር በክሱ የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ ከባድ የአታላይነት የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በአራተኛ ክስ ተከሳሾች ነፃ የተባሉ ሲሆን የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት በ1ኛ ክስ 1ኛ፣ 6ኛ፣ 12ኛ ተከሳሾች ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡
በ2ኛ ክስ 1ኛ፣ 6ኛ እና 12ኛ በተመሳሳይ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን በ3ኛ ክስ 6 ተከሳሾቸ ጥፍተኛ ተብለዋል፡፡
2ኛ ተከሳሽ በፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሃብት አስተዳደር ዳይሬክተር ፍቅሩ ኦላኒ በነፃ ተሰናብተዋል::
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት ቀሪዎቹ ተከሳሾች ላይ ባሳለፈው የቅጣት ውሳኔ 1ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ላይ 7 ዓመት ከ8 ወር ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፤ 6ኛ ተከሳሽ 14 ዓመት እስራት እና 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀጥተዋል፡፡
3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ ተሳሾች ላይ 6 ዓመት ፅኑ እስራት እና 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ሲወሰን በተመሳሳይ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾች 12 ዓመት ፅኑ እስራት እና 12 ሺህ የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።
በሲፈን መኮንን