የሀገር ውስጥ ዜና

ዕለታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያ ትክክለኛነት ወደ 80 በመቶ ከፍ ብሏል

By Abiy Getahun

July 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የዕለታዊ አየር ሁኔታ ትንበያ ትክክለኛነት 80 በመቶ ደርሷል አለ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የተቋሙ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የትንበያ ትክክለኛነት እየጨመረ መጥቷል።

የወቅቶች ወይም የረጅም ጊዜ ትንበያ ትክክለኛነቱ ወደ 78 በመቶ ያደገ ሲሆን የአጭር ጊዜ ወይም ዕለታዊ የትንበያ ትክክለኛነቱ ደግሞ ወደ 80 በመቶ ማደጉን አንስተዋል።

ተቋሙ ለትንበያ ስራው መረጃዎችን በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የአየር ሁኔታ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችና ከዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚጠቀምም ገልጸዋል።

በሚቲዎሮሎጂ አከፋፈል ሶስት ወቅቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ሀገራችን ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዝናብ መጠን የምታገኘው በክረምት ወቅት ነው ያሉት።

ባለፈው ግንቦት ወር በክረምት ስለሚኖረው የዝናብ ስርጭት ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤናና ለአካባቢ ጥበቃ የሚኖረውን ፋይዳ አስመልክቶ የትንበያ መረጃ መሰጠቱን አብራርተዋል።

ተቋሙ ወቅታዊና ፈጣን የአየር ሁኔታ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ከማድረስ አኳያ በክልሎች በሚገኙ 11 የሚቲዎሮሎጂ ማዕከላት ማህበረሰቡ በሚጠቀምበት ቋንቋ የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን እያቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

በሚዲያ ተቋማት፣ በኢንስቲትዩቱ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ወቅታዊና ፈጣን መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናት ለሚያደርጉ ዩኒቨርሲቲዎችና ግለሰቦች፣ ለአቪየሽን ዘርፍና በኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚሹ ድርጅቶች በዘርፉ የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ኢንስቲትዩቱ ያቀርባል ነው ያሉት።

ከ1 ሺህ 400 የሚቲዎሮሎጂ ጣቢያዎች እና ከ310 ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያዎች የሚሰበሰብ መረጃ ወደ ማዕከል ገብቶ በሳይንሳዊ ቀመር ተተንትኖ የትንበያ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምክረ ሃሳብ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።

በቴዎድሮስ ሳህለ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!