የሀገር ውስጥ ዜና

የአረንጓዴ አሻራ ለዘላቂ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው – ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

July 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለዘላቂ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው አሉ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ሠራተኞች ዛሬ ሰባተኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አከናውነዋል።

ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ የጎርፍ፣ ድርቅ፣ የአፈር መሸርሸርን ጨምሮ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ እንቅፋት የሚሆኑ ሳንካዎችን ፈጥሯል።

ለእነዚህና መሰል ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ ባደረገችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 40 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በአፍሪካም ሆነ በዓለም ምሳሌ የሚሆን ውጤት ተገኝቷል ያሉት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ÷ በመርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን አብራርተዋል።

በሀገር ደረጃ የሚተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡

ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች በስፋት እየተተከሉ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘው ሀገራዊ ግብ እውን እንዲሆን ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት መጥቀሳቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡

“በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሀሳብ ዘንድሮ እየተከናወነ ለሚገኘው ሰባተኛ ዙር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ስኬት ሁሉም የበኩሉን አሻራ እንዲያኖር ጥሪ አቅርበዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!