የሀገር ውስጥ ዜና

በድሬዳዋ ለአረንጓዴ አሻራ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኝ ለተከላ ዝግጁ ተደርጓል

By Melaku Gedif

July 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ፣ የደን ልማትና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 3 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለተከላ ዝግጁ ተደርጓል አለ፡፡

የባለስልጣኑ የደን ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተዘጋጅተዋል፡፡

ለዓመቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ፍራፍሬዎች፣ ጥምር ደን እና ሌሎችን ጨምሮ 4 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን አንስተዋል፡፡

እስካሁንም 3 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመው ÷ 3 ሚሊየን በላይ ጉዳጓድ መቆፈሩን አመልክተዋል፡፡

1 ሺህ 600 ሔክታር ቦታ ላይ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ÷ አሁን ላይ 1 ሺህ ሔክታር በላይ የሚሆነው ጂፒኤስ እና ካርታ ተዘጋጅቶለታል ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር 200 ሺህ በላይ ችግኞችን ለአጎራባች ክልሎችና ሀገራት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በአስተዳደሩ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በቅርቡ እንደሚጀመር ጠቁመው÷ ሕብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ