አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቻይና ቤጂንግ የኢትዮጵያን ባህል እና ኪነ ጥበብ ስራዎችን እያቀረበ የሚገኘው ኪን ኢትዮጵያ ቡድን የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት አግኝቷል።
ቡድኑ “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሐሳብ የኢትዮጵያን ባህል እና የኪነ ጥበብ ስራዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።
ቡድኑ የኢትዮጵያን ባህሎች፣ ሙዚቃዎች፣ የባህል አልባሳት፣ የፋሽን እና ዲዛይን ውጤቶች፣ አክሮባቲክስ እና ሌሎችንም የኪነ ጥበብ ስራዎች በማሳየት ላይ ሲሆን÷ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የፊት ገጻቸው ላይ ስራዎቻቸውን የሚያሳዩ ዘገባዎች በማውጣት ላይ ናቸው።
በቻይና የኢፌዴሪ ኤምባሲ ከባህል ቡድኑ ጋር በመሆን የኢትዮ-ቻይና የቢዝነስ፣ የባህል እና የኪነ ጥበብ ሳምንትን በቤጂንግ ማስጀመሩን እና የኢትዮጵያውያን የባህልና የኪነጥበብ ዝግጅቶች አስደናቂ መሆናቸውን ግሎባል ታይምስ ዘግቧል።
ሲጂቲኤን በበኩሉ÷ በቤጂንግ የኢትዮጵያ የባህል ትርኢት እየተካሄደ እንደሚገኝ እና በቀጥታ ስርጭት እንደሚያስተላልፈው በገጸ ድር ላይ ባጋራው መረጃ አመላክቷል።
በተመሳሳይ በቤጂንግ እየተካሄደ የሚገኘው የባህል እና ኪነ ጥበብ ስራዎች የቻይና እና ኢትዮጵያ 55ኛ ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማስመልከት መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶ የዘገበው የቻይናው ዜና አውታር ሺንዋ ነው።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር፣ የጋራ እሴቶችን ለማስተዋወቅ እንዲሁም የባህል ብዝኃነትን ውበት በዝግጅቱ ለማጉላት እንደምትፈልግ መግለፃቸውም በዘገባው ተመላክቷል።
በሶስና አለማየሁ