የሀገር ውስጥ ዜና

የኮሮና ቫይረስን ለመከለከል ተጀምረው የነበሩ መልካም ተግባራት መቀዛቀዝና መዘናጋት ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋናል- የጤና ሙያ ማህበራት

By Tibebu Kebede

August 13, 2020

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከለከል ተጀምረው የነበሩ መልካም ተግባራት መቀዛቀዝ እየፈጠረ ያለው መዘናጋትና መሰላቸት ውሎ አድሮ ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋናል አሉ የጤና ሙያ ማህበራ ።

አስራ አንድ የጤና ሙያ ማህበራት በዛሬው እለት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በወረርሽኙ መከላከል ላይ መንግስት የወሰዳቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች እናደንቃለን ያሉት አስራ አንዱ የጤና የሙያ ማህበራት በቀጣይ በቅንጅት ሊሰሩ ይገባቸዋል ያሏቸውን ነጥቦች በመግለጫቸው በዝርዝር አስቀምጠዋል።

በቀጣይ የሚከናወነው ሀገራዊ የኮቪድ 19 ምርመራ ዘመቻ በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ሊያስገኝ ስለሚችል መለስተኛ ወይም ምንም የበሽታውን ምልክት ያላሳዩ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ የሚደረግበት ስርዓት በጥንቃቄ እንዲመራ ጠይቀዋል።

ቀደም ብሎ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስገዳጅ የነበረ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ መቀዛቀዝ የታየበት የህዝብ መሰባሰብ ዋጋ እንዳያስከፍል ትኩረት እንዲያገኝም ጠይቀዋል።

ከእለት እለት በቫይረሱ የሚያዙ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ ስለሆነ የግል ደህንነት መጠበቂያ ቁሳቁስ ለባለሙያዎች እንዲቀርብም ነው ማህበራቱ  የጠየቁት።

እንዲሁም የጤና ሚኒስቴር ለህዝብ የሚያደርሰውን የ24 ሰዓታት የወረርሽኙን ሪፖርት አሁን ካለበት በተሻለ በዝርዝር እና በሚያስተምር መልኩ መቅረብ ይኖርታል ሲሉ የጤና ሙያ ማህበራቱ በመግለጫቸው አሳስበዋል።

በዘመን በየነ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።