የሀገር ውስጥ ዜና

በቡራዩ የውንብድና ወንጀል በመፈጸም የተከሰሱ ግለሰቦች በ18 እና 17 ዓመት እስራት ተቀጡ

By Abiy Getahun

July 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት በቡራዩ ክ/ከተማ በተለያዩ ግለሰቦች ላይ የውንብድና ወንጀል በመፈጸም የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በ18 እና 17 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ፡፡

የቅጣት ውሳኔ የተወሰነባቸው ተከሳሾች ወንድዬ ወይም ናቲ ከፍያለው እና ግርማ ወይም አስራት ቦጋለ በሚል ሁለት ስም ይጠቀሙ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ፣ ለ እና አንቀጽ 671 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ጠቅሶ ተደራራቢ ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህም በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በመጋቢት 2 ቀን 2017 ከቀኑ 8:00 ላይ በቡራዩ ከተማ በተለምዶ 105 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የመከላከያ አባል ሳይሆኑ ተመሳሳይ አልባሳት ለብሰው አባል ነን በማለት የውንብድና ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩና አምስት ግለሰቦችን በማስፈራራትና በማስገደድ የሞባይል ስልክን ጨምሮ የተለያየ ንብረት አስገድደው መውሰዳቸው በክሱ ላይ ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ በዚህ መልኩ የቀረበባቸውን የክስ ዝርዝር በችሎት ቀርበው እንዲደርሳቸውና በንባብ እንዲሰሙ ከተደረገ በኋላ የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው፤ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦባቸዋል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ በተገቢው ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ከዚህም በኋላ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ የመከላከያ አልባሳትን ለብሰው በቡድን የፈጸሙት ወንጀል መሆኑን እና አንደኛ ተከሳሽ ቀደም ሲል ጉዳዩ ከሚታይበት ችሎት ወጥቶ ለማምለጥ ሲሞክር በፀጥታ አካላት ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቅሶ ቅጣቱ ከብዶ እንዲጣልለት የቅጣት ማክበጃ አስተያየት አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ በዕርከን 40 መሰረት 1ኛ ተከሳሽ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ17 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaetertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!