ጤና

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ቁጥር 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ደረሰ

By Adimasu Aragawu

July 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሆኗል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ማህበረሰቡ የጤና መድኅን ሽፋን እንዲኖረው የተሰራው ስራ ውጤት አምጥቷል።

በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት የክልሉ ሕብረተሰብ የጤና መድኅን ሽፋን እንዲኖረው በተሰራው ጠንካራ ስራ 80 በመቶ ሕዝብ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አባል መሆን መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ የአባላት ቁጥር 859 ሺህ 385 መድረሱን ገልጸው÷ ከእነዚህ መካከል 252 ሺህ 901 የሚሆኑት መክፈል የማይችሉና በየደረጃው ባለ የመንግስት መዋቅር የተከፈለላቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሰዎች የጤና መድኅን ስርዓት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው÷ ከጤና መድኅን አባላት ከ624 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቦ ወደ ባንክ ገብቷል ብለዋል።

የጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ያልተቋረጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል በዞን ደረጃ የፋይናንስ ቋት ለመመስረት በተሰራው ስራ በሀላባ፣ የም እና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች ሙሉ ለሙሉ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ቀሪ ዞኖችም በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ትግበራ እንደሚገቡ ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

ይህም ከዚህ በፊት ይፈጠር የነበረውን የክፍያ እና ፋይናንስ ችግር በመፍታት ፍትሃዊና ያልተቆራረጠ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!