የሀገር ውስጥ ዜና

ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

By Abiy Getahun

July 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል አሉ።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት 2ኛ የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በአሶሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ለምክር ቤቱ የመንግስት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ጎልተው የታዩበት ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት በክልሉ በነበረው ችግር የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በማቋቋም ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት ሁሉንም አማራጭ በመጠቀም ሰላም ማስፈኑን አንስተዋል።

አርሶ አደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነቱን አሳድጓል ያሉት አቶ አሻድሊ፤ በ2016/17 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ 40 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ነው ያሉት።

የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ልማት በመቀየር ተጨባጭ ውጤት መታየቱን ገልጸው፤ 4 ሺህ 767 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በዘርፉ ላይ ሰፊ ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን ገልጸዋል።

የአሶሳ ከተማ የ9 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ እና የ9 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ግንባታ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸው የመንግስት እና የሕብረተሰቡ የጋራ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም ተጨማሪ መሠረተ ልማቶችን ለማከናወን አቅም እንዳለን የሚያሳይ ተግባር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በገቢ ዘርፍ 4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 5 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ስራ 51 ሚሊየን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን ጠቁመው፤ ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ተቋማት ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ የአሰራር ክፍተቶች እንዲታረሙ መደረጉን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሌማት ትሩፋት፣ አረንጓዴ ዐሻራና ሌሎች ሀገራዊ የልማት ኢኒሼቲቮች በክልሉ በስፋት የተተገበሩበትና ውጤታማ የሆኑበት ነው ብለዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!