አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል 1 ነጥብ 1 ሚሊየን የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት አቶ አረጋ ከበደ፤ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በእልህና በቁጭት ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ሰላምና ልማት ወዳድነቱን በግልፅ አሳይቷል ነው ያሉት።
ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ፣ ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛንን ለማስጠበቅ እንዲሁም የመንግስት ወጪ እና ገቢን ለማመጣጠን በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለማቃለል በየዘርፉ ከተሠሩ ሥራዎች በተጨማሪ 1 ቢሊየን ብር ያህል የመንግሥት ተዘዋዋሪ በጀት ተመድቦ መሠራቱን አንስተዋል።
የሥራ አጥነት ችግርን ለመቀነስ ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ያስገባ እቅድ ተዘጋጅቶ በመሰራቱ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ 817 ሺህ 41 የሚሆነው ቋሚ የሥራ እድል መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥም 64 ሺህ 820 የሚሆነው በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንደሆነ ገልጸዋል።
በግብርና ዘርፍ ውጤታማ አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተው፤ በ2016/17 የምርት ዘመን በመደበኛና በገበያ ተኮር የመኸር ሰብሎች 5 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ 170 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ነው ያሉት።
ከገቢ አንጻር ከታቀደው አጠቃላይ 71 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር በ11 ወር ውስጥ ከ45 ቢሊየን በላይ ብቻ መሰብሰቡን አንስተው፤ የገቢ አሰባሰብ ሥራው አዝጋሚ መሆኑን ተናግረዋል።
የገቢ አሰባሰብ ሥራው ያሉበትን ተግዳሮቶች በመለየት የገቢ ተቋሙን አቅም በቴክኖሎጅና በሰው ኃይል በማጠናከር እና ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት በአዲሱ በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ተብሏል።
በደሳለኝ ቢራራ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting Telegram t.me/fanatelevision Website www.fanamc.com TikTok www.tiktok.com/@fana_television WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29 Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!