አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የሥርዓተ ምግብ ጉባዔው ከሌሎች ሀገሮች የምንማርበት እና እኛም ደግሞ ወደ ተግባር የተሸጋገርንበትን መንገድ ለሌሎች የምናሳይበት ትልቅ ፋይዳ ያለው ዝግጅት ነው አሉ።
ሚኒስትሯ ከፋና ሚድያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ጉባኤው የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ጉዳዮችን በስፋት የሚዳስስ ትልቅ ጉባዔ ነው።
በፈረንጆቹ 2021 በተደረገው የመጀመሪያው ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ የምግብ ሥርዓት ጉዳይን በዕቅድ ውስጥ በማስገባት ልትተገብራቸው ቃል ከገባችባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በተከታታይ የተሰሩት ስራዎች በአሁኑ ጉባዔ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ለመተግበር ወሳኝ እንደሆኑ አመላክተዋል።
ምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ለጤና ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ በሥርዓተ ምግብ ውስጥ ያለፈ ትውልድ ጤናማ እና ምርታማ እንዲሁም ትልቅ ውጤት ማምጣት የሚችል ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በዚህ ውስጥ “ከእርሻ እስከ ጉርሻ” በሚል ሀሳብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ባለድርሻዎችን በማሳተፍ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እንደተሰሩ አመልክተዋል።
ምግብ እና ሥርዓተ ምግብን ከግብርና አንፃር ብቻ ሳይሆን ከጤና አንጻር አንድ ላይ ተያይዞ ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ይህ ጉባዔ ከሌሎች ሀገሮች የምንማርበት፣ እንዲሁም እኛም ደግሞ ከቃላት ወደ ትግበራ የተሸጋገርንበትን መንገድ ለሌሎች የምናሳይበት ትልቅ ፋይዳ ያለው ዝግጅት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ታስተናግዳለች።
በዮናስ ጌትነት