ስፓርት

አርሰናል ቪክተር ጎከሬሽ ማስፈረሙን ይፋ አደረገ

By Yonas Getnet

July 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አርሰናል ከብዙ የዝውውር ውጣ ውረድ በኋላ ስዊድናዊውን የፊት መስመር አጥቂ ቪክተር ጎከሬሽ ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል፡፡

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ለ27 ዓመቱ ተጫዋች 63 ሚሊየን ዩሮ እንዲሁም እየታየ በሚጨመር 10 ሚሊየን ዩሮ ዋጋ ነው ተጫዋቹን ከስፖርቲንግ ሊዝበን ያስፈረመው፡፡

ባለፈው የውድድር ዓመት ብቻ 54 ግቦችን ያስቆጠረው ጎከሬሽ፤ በመድፈኞቹ ቤት ለአምስት ዓመታት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።

ተጫዋቹ በአርሰናል ቤት ትልቅ ቦታ ያለውን 14 ቁጥር ማልያ የሚለብስ ይሆናል።

ተጫዋቹ ከበርካታ ክለቦች ጥያቄ ሲቀርብለት የነበረ ሲሆን፤ ምርጫው አርሰናል ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ወደ ክለቡ ለመዘዋወር ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።