አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማዕከል አድርጋ እየሰራች ነው አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)።
2ኛው የተባበሩት መንግሥታት ሥርዓተ ምግብ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
“ወጣቶች እንደ ለውጥ ፈጣሪ፥ ጥበብና ፈጠራ ለለውጥና ዘላቂ የምግብ ስርዓት ያላቸው ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የጉባኤው አካል የሆነ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠችና ሰፊ የስራ ዕድል እየፈጠረች ትገኛለች።
በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርና የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ወጣቶችን በንቃት በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።
በግብርናው ዘርፍ ለሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ለግብርና ቴክኖሎጂና ወጣቶች በምግብ ስርዓት ላይ ያላቸውን ሚና ማሳደግ በጉባኤው ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።
የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሃመድ በበኩላቸው፥ በዓለም የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የምግብ ስርዓት ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን አንስተዋል።
ለችግሮች መፍትሄ በመስጠት የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦችና የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ለወጣቶች ብልጽግናና ስራ ፈጠራ ከፖሊሲ ጀምሮ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ፥ በጣልያን እና በተመድ ትብብር የተዘጋጀው ሁለተኛው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ዋና ዓላማው የዓለም የምግብ ሥርዓትን ማሻሻል ነው።