አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለዓለም የምግብ ስርዓት መረጋገጥ ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡
2ኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ጉባኤ ማጠቃለያ እየተካሄደ ነው።
ፕሬዚዳንቱ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ዓለም ለምግብ ስርዓት መሻሻል የጋራ ጥረቶችን ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቅሰው፥ የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት የሚቻለው በጋራ ቅንጅት መሆኑን አብራርተዋል።
ዓለማችን የ2 ቢሊየን ዜጎችን የምግብ ስርዓት እንዲያሻሽል በአዲስ አበባው ጉባኤ የተነሱ አጀንዳዎች ወደ ተግባር እንዲገቡ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ለዚህም መንግስታት፣ ኢንቨስተሮች፣ ሲቪል ማህበራት እንዲሁም ወጣቶችን ያሳተፉ የጋራ ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግርና ሉዓላዊነት እንዲሁም የምግብ ዋስትና በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል የተደረጉ ጥረቶችንና ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ወደ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አንስተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የ2030 ዘላቂ የልማት ግብ እንዲሳካና ማህበራዊ ለውጥ እንዲመጣ ሀገራት ያደረጉት ጥረትና ያሳኩት ሊደነቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የምግብ ስርዓት አጀንዳ ክብር፣ ነፃነትና ለሰው ልጆች ፍትህን የመመኘት ውጤት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ በዓለም ላይ በመስኖ ልማት፣ በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ የተሰሩ ስራዎች የተሳካ ፖሊሲ ውጤት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሰለሞን በየነ