አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አረንጓዴ አሻራ ለተፈጥሮ ሰላምና ደህንነት የሚሆን ብርቱ ሰልፍ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመስገን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ጋር በመሆን በክልሉ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የመትከል ማንሰራራት ጉዟችን ዛሬም በታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛና በወርቋ ምድር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ስራችን ምግብ የምናመርትበት፣ በቅጠሎቹ በረሃማነትን፣ በስሮቹ ደግሞ የአፈር መሸርሸርን የምንከላከልበት ጋሻችን ነው ብለዋል።
ዛሬ የተከልናቸው ችግኞች ከጥላነት የተሻገረ ፍሬ የሚሰጡ፣ ከዛፍነትም ያለፉ የውሃችን ጠባቂ ዘብ ናቸው ሲሉም ነው በመልዕክታቸው ያሰፈሩት፡፡
በተጨማሪም በአሶሳ ከተማ ዛሬ የጎበኘናቸው የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገፅታ፣ ዘመናዊነትና የነዋሪዎቿን ኑሮ የሚያሻሽሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡