አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዩራጋይ ራሷ ያዘጋጀችውን የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ በፍጻሜው አርጀንቲናን በማሸነፍ ራሷ በማንሳት የመጀመሪያዋ ሀገር የሆነቸው በዛሬዋ ዕለት በፈረንጆቹ 1930 ነበር፡፡
13 ሀገራትን ያሳተፈው የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ በዩራጋይ አስተናጋጅነት በዋና ከተማዋ ሞንቴቪዲዬ ከፈረንጆቹ ሀምሌ 13 እስከ ሀምሌ 30 መካሄዱን ታሪክ ያስታውሳል፡፡
ውድድሩ በመጀመሪያ 16 ብሄራዊ ቡድኖች እንዲሳተፉበት ቢታቀድም 16 መድረስ ባለመቻሉ በ13 ብሄራዊ ቡድኖች መካከል የመጀመሪያው ዓለም ዋንጫ ውድድር ተካሂዷል፡፡
በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ባለው ረጅም ጉዞ እና ውድ የመርከብ ወጪ ምክንያት አራት የአውሮፓ ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ተሳትፈዋል፡፡
የዩራጋይ እግር ኳስ ማህበር የተወሰነ የአውሮፓ ተሳትፎን ለማግኘት ሲል ለእንግሊዝ፣ ሰሜን አየርላንድ፣ ስኮትላንድ እና ዌልስ ብሄራዊ ቡድኖች የግብዣ ደብዳቤ ልኳል።
ግብፅ ብቸኛዋ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድን የነበረች ቢሆንም በሜዲትራኒያን ባህር ላይ በተነሳ አውሎ ንፋስ ዩራጋይ ለመድረስ ከመዘግየትም ባለፈ ወደ ዩራጓይ የምትጓዝበትንም መርከብ ማጣቷም ይነገራል፡፡
ጣሊያን፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስፔን፣ ሃንጋሪ እና ዩራጋይ ውድድሩን ለማዘጋጀት ማመልከቻ ያስገቡ ሲሆን፥ የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ የማዘጋጀት ዕድል ያገኘችው ዩራጋይ ነች፡፡
ከደቡብ አሜሪካ አዘጋጇ ሀገር ዩራጋይ፣ አርጀንቲና፣ ቦሊቪያ፣ ብራዚል፣ ቺሊ፣ ፓራጓይ እና ፔሩ ሲሳተፉ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ሮማኒያ እና የያኔው ዩጎዝላቪያ ከአውሮፓ እንዲሁም ሜክሲኮና አሜሪካ ደግሞ ከሰሜን አሜሪካ በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡
ብሄራዊ ቡድኖቹ በአራት ምድብ የተከፋፈሉ ሲሆን፥ ከየምድቡ 1ኛ ሆነው የሚያልፉ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፉ ሲሆን በዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ፈረንሳዊው ሉሲን ሎረንት ነበር፡፡
በዚሁ የውድድሩ ህግ መሰረት በየምድባቸው አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፍ የቻሉት ደግሞ አርጀንቲና፣ ዩራጓይ፣ አሜሪካ እና ዩጎዝላቪያ ነበሩ፡፡
በፍጻሜው ጨዋታ ልክ በዛሬዋ ዕለት በፈረንጆቹ 1930 አስተናጋጇ ሀገር ዩራጓይ ከ68 ሺህ በላይ ደጋፊዎች ፊት አርጀንቲናን 4 ለ 2 በማሸነፍ የዓለም ዋንጫን በማንሳት የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች፡፡
ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ባደረጉት ክርክር በመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ሁለት ኳሶችን ተጠቅመዋል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ የአርጀንቲና ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ የዩራጋይ ኳስ ተጠቅመው የፍጻሜ ፍልሚያቸውን አድርገዋል፡፡
ስታዲዮ ሴንቴናሪዮ፣ ስታዲዮ ፖሲቶስ እና ስታዲዮ ግራን ፓርኪ ሴንትራል በዓለም ዋንጫው ግልጋሎት የሰጡ ስታዲየሞች ሲሆኑ፥ 90 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ስታዲዮ ሴንቴናሪዮ የተገነባው ለውድድሩና ለዩራጋይ የነጻነት 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ነበር።
ስታዲየሙ የግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎችን ጨምሮ ከ18ቱ ጨዋታዎች 10 ጨዋታዎችን አስተናግዷል፡፡
በፈረንጆቹ 2030 የፊፋ የዓለም ዋንጫን ስፔን፤ፖርቹጋል እና ሞሮኮ በጋራ የሚያዘጋጁት ሲሆን የመክፈቻ ጨዋታው በዩራጋይ ስታዲዮ ሴንቴናሪዮ ስታዲየም ሲካሄድ የዓለም ዋንጫ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ያከብራል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ